የስራ አካባቢ ደህንነት የሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 45001 work place safety management system) ለምን ያስፈልጋል?

በዓለማችን ማንኛውም ሠራተኛ፣የስራ መሪም ሆነ ባለሀብት እንዲፈጠር የሚፈልጉት የጋራ ጉዳይ ቢኖር በስራ አካባቢ የሚከሰት አደጋ እንዲቀነስና የተሻለ የሥራ ቦታን እንዲፈጠር ነው።በመሆኑም ይህንን የጋራ ጉዳይ ለማሳካት ታቅዶ የተዘጋጀውን የስራ አካባቢ ደህንነት የስራ አመራር ስርዓት (ISO 45001 work place safety management system) በመተግበር እንዴት የሥራ ላይ አደጋን መቀነስና የተሻለ የሥራ አካባቢ መፍጠር እንደሚቻል መመልከቱ ተገቢ ነው።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በቀን ውስጥ በየ15 ደቂቃው ቢያንስ አንድ ሠራተኛ ከስራ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር አደጋ ወይም በሽታ የሚሞት ሲሆን 153 ሠራተኞች ደግሞ ከስራ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር አደጋ አካል ጉዳተኛ ይሆናሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ከሥራ ደህንነት ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ አደጋዎች በዓመት 2.8 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ይመዘገባል። ይህ ደግሞ በተቋምና በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።

ሆኖም ግን ይህን ችግር ሊፈታ የሚችል የአመራር ስርዓት መዘርጋት የሚፈጠረውን አደጋ ለመቆጣጠር አይነተኛ መፍትሔ በመሆኑ የሥራ አካባቢ ደህንነት ሥራ አመራር ስርዓት (ISO 45001 Work Place Safty Management System) መገንባት አስፈላጊ ይሆናል። በመሆኑም ለሁሉም ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች የአሰራር ስርዓቱን መተግበር ለሠራተኞች ለሥራ ምቹ የሆነ አካባቢ ከመፍጠሩም ባሻገር በሥራ ቦታ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመከላከል ያስችላል።

በተጨማሪም በአምራች ወይም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስርዓቱ ከተዘረጋ ለሠራተኞች መልካም የስራ አካባቢ እንዲፈጠር መሰረት የሚጥል ሲሆን ለባለሀብቱ ደግሞ በስራ ላይ ለሚፈጠሩ አደጋዎች የሚያወጣውን አላስፈላጊ ወጪ በመቀነስ ምርታማነት እንዲጨምር ይረዳል። ስለዚህ ይህ የአሰራር ስርዓት በዓለም አቀፉ የንግድ መድረክ ተወዳድሮ ለማሸነፍ እንደ አንድ መሳሪያም የሚያገለግል ስለሆነ የአሰራር ስርዓቱን መትከል የተቋምን ህልውና አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ይከላከላል።

ይህ ደረጃ ከጥራት ሥራ አመራር ስርዓት (ISO፡9001 Quality Management System) እና ከአካባቢ ደህንነት ሥራ አመራር ስርዓት (ISO 14001 Environmental Managmnet System)የአሰራርስርዓቶችጋርተመጋጋቢና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ያለምንም ችግር ቀላል በሆነ መንገድ ተሳስሮ ሊተገበር የሚችል ሲሆን ደረጃው በሥራ አካባቢ ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚደርሱ አደጋዎችን በመለየት የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ለማስወገድ የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች የሚያመላክት የሥራ አመራር ስርዓት እንጂ በምርት አጠቃቀምና ጥበቃ ላይ ያተኮረ አይደለም። በተጨማሪም ይህ የአሠራር ሥርዓት ከሌሎች በተቋሙ በትግበራ ላይ ካሉ ደረጃዎችና ሰነዶች ጋር የሚጣረስ ሣይሆን በቅንጅት ለመተገበር የበለጠ ዕድል የሚሰጥ ነው። ስለሆነም ደረጃው ተዓማኒነት ከመፍጠሩም ባሻገር የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማሳካት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

(ምንጭ     ISO focus November 2015 edition page 40)