በባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ደግሞ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለቱ ውስብስብ በሆነ መንገድ በመጨመሩና አብዛኞቹ የምግብ ምርቶችም ድንበር ተሻጋሪ ስለሆኑ ለምግብ ማጭበርበር ወንጀል መበራከት እድል ከፍቷል። እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ገለጻ ምግቡ ለጥቅም ከመዋሉ በፊት እስከ 10‚000 ማይልስ ይጓጓዛል። ይህም ማለት ምግቡ ከምርት እስከ ገበታ ረዥም ሂደትን ስለሚጠይቅና የላላ የቁጥጥር ስርዓት ስላለ ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀል፣ የመበከልና የጥራት መጓደል ችግር ያጋጥመዋል። ይህም በማደግ ላይ ያለውን የህዝብ ቁጥር፣ ከምጣኔ ሀብት እድገት ጋር በተያያዘ ለተፈጠረ የፍላጎት መጨመር እንዲሁም ድንበር ዘለልነት በመፈጠሩ ሀገራት የሕብረተሰባቸው ጤና አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸውን ደረጃዎች መሰረት አድርገው የሦስተኛ ወገን የፍተሻ ላቦራቶር አገልግሎት ከሚጠቀሙ አምራቾች ግብይት እንዲፈጽሙ አስገድዷል። ከኢኮኖሚም አንፃር በምግብ ላይ የሚፈጠር የጥራት መጓደል የማጭበርበር ወንጀል ላኪና አስመጪዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ 15 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በዓመት ያስወጣል።

በምግብ ደህንነት ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮች እጅግ ጥልቅ፣ ሰፊና ውስብስብ ከመሆናቸው ባሻገር የሸማቹን የመግዛት አቅም ያማከለና ጥራት ያለው ምርት ከማቅረብ አኳያ በመንግስትና በተቆጣጣሪ አካላት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል።

ስለሆነም ተጠቃሚው ሕብረተሰብ በሚሸምተው የምግብ ምርት ደህንነትና ይዘት ላይ እምነት እንዲኖረው ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለውን የምግብ ደህንነት የስራ አመራር ስርዓትን (ISO 22000 food safty management system) መሰረት አድርገው የተስማሚነት ምዘና አገልግሎቶችን በሚከውኑ ተቋማት ተፈትሸው የተረጋገጡ ምርቶችን እንዲሸምቱ እንዲሁም አምራች ድርጅቶች ለምርቶቻቸው የሦስተኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬትን ተጠቃሚ እንዲሆኑና ከተቋማቱ ጋርም መረጃ በመለዋወጥና የአሰራር ስርዓቱንም በመዘርጋትና በመጠቀም የምግብ ጥራት መጓደል ችግርን መቅረፍ ይቻላል።

የምግብ ጥራትና ደህንነትን የማረጋገጥ ተግባር ቀላል ባለመሆኑ ሸማቹን በዚህ ዙርያ ማሳተፉ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ አምራቹ የምግብ ደህንነት የስራ አመራር ስርዓትን (ISO 22000 food safty management system) እንዲተገብር ማድረጉ የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ ጠቃሚ ነው። ሆኖም ግን ይህንን የማስፈፀም ስራ ለተቆጣጣሪ አካላት ብቻ የሚተው ሣይሆን የተጠቃሚውን ግንዛቤም ማሳደጉ መሰረታዊ ነው።

በተጨማሪም የምግብ ደህንነት የስራ አመራር ስርዓት (ISO 22000 food safty management system) ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ደረጃ በመሆኑ ሆን ተብሎም ሆነ በስህተት ለሚፈጠር የምግብ መበከልን እንዳይፈጠር ስለሚያግዝ መተማመን በመፍጠር የኢኮኖሚ ጠቀሜታን ያጎለብታል።

(ምንጭ፡ ISO focus July-Aug 2016 edition page 12)